የምንኖረው በተሳሰረ የከተማ መልከዓ ምድር ላይ በመሆኑ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የምንጓዝበት መንገድ ለአኗኗር ዘይቤያችን መሠረታዊ ነገር ነው። የምንጓዘው ወደ ሥራ ለመሄድም ይሁን ሸቀጣ ሸቀጦችን ለመግዛት፣ ጓደኞቻችንን ለመጠየቅ ወይም ደግሞ ልጆችን ለማሳፈር የትራንስፖርት አገልግሎቱ አሁን ካለንበት ቦታ ተነስተን መሄድ ወደምንፈልግበት ቦታ እንድንደርስ ማድረግ የሚያስችል አገናኝ መስመር ነው። በመሆኑም ሁላችንም ደኅንነታቸው በተጠበቁ፣ ቅልጥፍና በተሞላባቸው እና ለከባቢ አየር ተስማሚ በሆኑ የትራንስፖርት አማራጮች መጓጓዝ መቻል ይገባናል።
Cambridge ውስጥ ብዙ አስደሳች ነገሮች አሉ። በሀገሪቷ ውስጥ ለእግር ጉዞ እጅግ አመቺ ከተማ ተብለን ተሰይመናል። Walk Score ከዚህም አልፎ በእያንዳንዱ ምድብ ከMassachusetts ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበች "የእግረኞች ገነት” እና “የብስክሌት ነጂዎች ገነት” በማለት ለCambridge እውቅና ሰጥቷል። በPeopleforBikes የቅርብ ጊዜ ደረጃዎች መሠረት Cambridge ከ604 መካከለኛ መጠን (ከ50ሺህ እስከ 300ሺህ የሕዝብ ብዛት) ያላቸው የU.S. ከተሞች መካከል ብስክሌት ለመንዳት ባላት አመቺነት ከDavis፣ California ቀጥሎ 2ኛ ደረጃን ይዛለች። አምስት የRed Line ማቆሚያዎችን፣ አዲስ የታደሰው በLechmere የሚገኘውን Green Line ጣቢያ፣ Commuter Rail፣ 26 የMBTA አውቶቡስ መስመሮችን እና በርካታ ለሕዝብ ተደራሽ የሆኑ ማመላለሻዎችን ጨምሮ ብዙ የሕዝብ መጓጓዣ አማራጮች አሉን።
ይሁን እንጂ ብዙ አሳሳቢ ጉዳዮችም አሉ። ከወረርሽኙ ወዲህ ትራፊክ እና የመንገድ መጨናነቅ ጨምሯል። ተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት ዓይነቶችን በመጨመራችን ምክንያትም መንገዶቻችን ለመንቀሳቀስ ውስብስብ ሆነዋል። ብስክሌት መንዳትን ይበልጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ ያደረግን ቢሆንም ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ሶስት ብስክሌተኞች በጎዳናዎቻችን ላይ ሕይወታቸው አልፏል፤ ይህም ክስተት በማኅበረሰባችን ውስጥ ትልቅ ክፍተት እንዲኖር ያደረገ፣ አሁንም ገና ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅብንም እንድናስታውስ ያደረገን ክስተት ነው። እንዲሁም በከተማዋ ዙሪያ መጓጓዝ ወይም አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ከአረጋውያን እና ከአካል ጉዳተኛ ነዋሪዎቻችን እየሰማን ነው።
ይህ እትም ከጎዳናዎቻችን ጋር ተያይዞ ያሉትን ተፃራሪ ተግዳሮቶች እንዴት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት እየሞከርን እንደሆነ ያሳያል። ለጉዳዩ ቀላል መፍትሄዎች የሉም፤ ነገር ግን እነዚህ ታሪኮች ሁሉም ነዋሪዎቻችን ይበልጥ ደኅንነታቸው በተጠበቁ፣ ቅልጥፍና በተሞላባቸው እና ለከባቢ አየር ተስማሚ በሆኑ የትራንስፖርት አማራጮች መጓጓዝ እንዲችሉ እንዴት እየሠራን እንደሆነ ያሳያሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።