ጥያቄ፦ ስለ በጀት ሂደቱ እና ምን ዓይነት መልክ እንዳለው ጥቂት ሊነግሩን ይችላሉ?
Yi-An Huang፦ የበጀት ሂደቱ የአጋርነት ሥራ ሲሆን፣ እኔም ከCity Council (ከተማ ምክር ቤቱ) እና ከፋይናንስ ሊቀመንበራችን Patty Nolan ጋር ላለው አጋርነት አመስጋኝ ነኝ። በየዓመቱ በጀቱ ላይ የበለጠ ግልጽነት ለማምጣት ስንሠራ ቆይተናል፦ ሂደቱን ቀደም ብሎ መጀመር፣ በአካባቢያችን ያለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ የሚደረጉ ግምገማዎችን ጨምሮ ያሉንን የረጅም ጊዜ ትንበያዎች መወያየት እና የመንግሥት ዶላር እንዴት ወጪ እየተደረገ እንደሆነ ለመገምገም ለሕዝብ ክፍት የሆኑ የበጀት ስብሰባዎችን ማካሄድ።
ይህን ሂደት ተከትሎ City Council ጁን 2 ላይ የ2026 ዓ.ም በጀት ዓመትን በጀት አጽድቋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ጠንካራ ሥራ ለሠሩት City Council፣ የማኅበረሰብ አባላት እና ሠራተኞች ምስጋናዬን አደርሳለሁ።
ጥያቄ፦ በዚህ ዓመት የበጀት አወጣጥ ሂደት ውስጥ በተለየ መልኩ ተጽዕኖ የነበራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
Yi-An Huang፦ እንደ ከተማ እያጋጠመን ካለው ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት አንፃር አስቸጋሪ በጀት ነበር። አዲሱ የፌደራል አስተዳደር ሥራ ከመጀመሩ በፊትም ቢሆን፣ በመላው ክልል የሚታየው እድገት እየተዳከመ ሲመጣ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው አቅጣጫ ሊቀይር እንደሚችል የከተማ አስተዳደሩ ተንብዮ ነበር። ይህም በከፍተኛ የወለድ ተመኖች፣ ከፍተኛ የግንባታ ወጪዎች እና እየበዙ ያሉ ሥራ የማይሠራባቸው ክፍት የቢሮ እና የላቦራቶሪ ሥራ ቦታዎች ምክንያት የመጣ ነበር። ነባር ፕሮግራሞችን የማስቀጠል እና አዲስ ተነሳሽነቶች ላይ ኢንቨስት የማድረግ ችሎታችን የፋይናንስ ጥንካሬያችንን በመጠበቅ ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ ምክንያት ለወደፊት የበጀት እድገት ዒላማዎች ለማስቀመጥ ተስማምተናል።
በተጨማሪም የፌደራል ARPA ፕሮግራም ደረጃ በደረጃ እየተዘጋ ነው። ይህ የወረርሽኝ የገንዘብ ድጋፍ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች ከሚላክ ገንዘብ ጀምሮ እስከ የቤት አልባ ግለሰቦች አገልግሎቶች፣ መጠለያ እና አዲስ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ፕሮግራሞች ድረስ ኢንቨስት ለማድረግ ለከተማ አስተዳደሩ እና ለማኅበረሰብ አጋሮች $88 ሚሊዮን አቅርቧል። ሆኖም የፕሮግራሙ ስፋት ከተማ አስተዳደሩ ጉድለቶችን ለመተካት ካለው አቅም የበለጠ በመሆኑ፣ በመጪው ዓመት ውስጥ አብዛኛው ገንዘብ ጥቅም ላይ ውሎ ያልቃል።
ጥያቄ፦ የ2026 ዓ.ም በጀት ዓመት በጀት ለዚህ ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣል?
Yi-An Huang፦ የ2026 ዓ.ም በጀት ዓመት የበጀት እድገት ቁጥጥርን መኖሩን ያንፀባርቃል። በፎል (መኸር) ወቅት ከCity Council ጋር ውይይት የተደረገበትን የበጀት እድገት ቁጥጥር ግብ በመምታት በ2026 ዓ.ም በጀት ዓመት በ3.8% ያደገ በጀት አጽድቀናል። የ2025 ዓ.ም በጀት ዓመት ላይ ከነበረው 8.1%፣ የ2024 ዓ.ም በጀት ዓመት ላይ ከነበረው 7.2% እና የ2023 ዓ.ም በጀት ዓመት ላይ ከነበረው 7.1% እድገት ጋር ሲነፃጸር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። ሆኖም የበጀት እድገትን በምንቆጣጠርበት ጊዜ የከተማ አስተዳደሩ ሲደግፍ የቆየውን ወሳኝ ኢንቨስትመንቶች እና ፕሮግራሞች እየደገፍን እንቀጥላለን። ከዚህ ጋር ተያይዞም ምክር ቤቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ላይ የሚውል ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አስቀጥለናል። ለ2026 ዓ.ም በጀት ዓመት የታቀዱት ወጪዎች ተመጣጣኝ ዋጋ ላላቸው መኖሪያ ቤቶች የሚውል የ$50 ሚሊዮን የገንዘብ ድጋፍ፣ ለቤት አልባነት መፍትሄዎች የሚውል $18 ሚሊዮን፣ ለኢኮኖሚያዊ እኩልነት እና ዕድል የሚውል $17 ሚሊዮን፣ ለአየር ንብረት Net Zero (ምንም በካይ የማያመነጭ) ግቦቻችን የሚውል $18 ሚሊዮን፣ አየር ንብረት ለውጦችን የመቋቋም አቅም ላይ የሚውል $21 ሚሊዮን ዶላር፣ ለሁለንተናዊ pre-kindergarten የሚውል $35 ሚሊዮን እና ሌሎች በርካታ ተጨማሪ ነገሮችን ያካትታሉ።
ጥያቄ፦ መጀመሪያ የቀረበው የ2026 ዓ.ም በጀት ዓመት በጀት ስሪት ላይ የተደረጉት ለውጦች ምንድን ናቸው?
Yi-An Huang፦ ይህ በጀት ምክር ቤቱ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት የተደረጉትን ለውጦች ያንፀባርቃል። Transition Wellness Center የተሰኘውን የቤት አልባ ግለሰቦች መጠለያ ለመዝጋት የታቀደ እንደመሆኑ መጠን፣ ምክር ቤቱ የቤት አልባ አገልግሎቶች ላይ የሚያስፈልገው ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ዙሪያ ከፍተኛ ስጋት እንዳለው አንስቶ ነበር። ለምክር ቤቱ ግብረ መልስ ምላሽ ለመስጠት ተጨማሪ የማዘጋጃ ቤት መኖሪያ ቤት ቫውቸሮችን ለመፍጠር በጀቱ ላይ $1 ሚሊዮን ጨምረናል። እነዚህ ቫውቸሮች ተጨማሪ ሰዎችን ከቤት አልባነት ለማውጣት እና ወደ ቋሚ ድጋፍ ሰጪ መኖሪያ ቤቶች ለማሸጋገር የሚረዱ ሲሆን፣ ይህ ለውጥ የማዘጋጃ ቤት ቫውቸሮችን ሙከራ ላይ ለማዋል ምክር ቤቱ ያሳየውን ፍላጎትም ያሟላል። ይህ የገንዘብ ድጋፍ በመላው ከተማ በጠቅላላው 96 አዲስ ቋሚ ድጋፍ ሰጪ መኖሪያ ቤቶችን የገነቡ ሶስት ፕሮጀክቶች በገንዘብ ከደገፍንበት በAffordable Housing Trust (ተመጣጣኝ ዋጋ ላላቸው መኖሪያ ቤቶች የሚሆን ፈንድ) ኢንቨስት የተደረገ ከ$18 ሚሊዮን በላይ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ነው።
እንዲሁም $5 ሚሊዮን ትርፍ በጀት ለፌደራል የድጎማ ገንዘብ ማረጋጊያ ፈንድ መድበናል። ይህ ለውጥ የተደረገው በተለይ እጅግ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን የሚያገለግሉ ፕሮግራሞች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ከፌደራል መንግሥት የሚመጡ የገንዘብ ድጋፍ ቅነሳዎች የሚፈጥሩትን ከፍተኛ ስጋት በመገንዘብ ነው።
ጥያቄ፦ የዚህ ዓመት የበጀት ሂደት ዙሪያ የሚያካፍሉን ሌላ አስተያየት አለዎት?
Yi-An Huang፦ ለከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እና ሠራተኞች እንዲሁም ለበጀት ፋይናንስ ቡድን በዚህ ሂደት ውስጥ ለሠሩት ሥራ በሙሉ እና ለCity Councilም ይበልጥ ግልጽ እና አሳታፊ ሂደት መገንባት በመቻላችን ምስጋናዬን አቀርባለው። ወደ መጪው ዓመት በምንሸጋገርበት ጊዜ ሊመጡ የሚችሉትን የፌደራል ገንዘብ ድጋፍ ለውጦች እና ማኅበረሰባችን ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን ተጽዕኖ ስንገመግም የምክር ቤት እና የማኅበረሰብ ውይይቶችን ቀደም ብሎ እና በየጊዜው ማካሄድ ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናል። እናም እንደ ሌሎች ጥረቶቻችን ሁሉ፣ ተግዳሮቶችን አብረን እንታገላለን።