ለልጅዎ የመኪና መቀመጫ እንዴት መግጠም እንደሚችሉ ወይም በትክክል መግጠም አለመግጠምዎ እያሳሰብዎ ነው? የCambridge Police Department (የCambridge የፖሊስ አገልግሎት መምሪያ) እርዳታ ለመስጠት ይገኛል። አንድ መኮንን ለማንኛውም የCambridge ነዋሪ የልጅ የመኪና መቀመጫ ፍተሻ የሚያደርጉበት እና አግባብ የሆነውን አገጣጠም የሚያስተምሩበት በነፃ የሚሰጥ የተሳፋሪ ልጅ ደኅንነት ሥልጠና ያቀርባሉ።
የልጅ የመኪና መቀመጫዎችን፣ ልጁን ከፍ የሚያደርጉ (ቡስተር) የመኪና መቀመጫዎችን እና የደኅንነት ቀበቶዎችን በአግባቡ መግጠም እና መፈተሽ የከፍተኛ ጉዳት ወይም የሞት ስጋቶችን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳሉ። Centers for Disease Control and Prevention (የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከያ ማዕከል፣ CDC) እንደገለጸው፣ የልጅ የመኪና መቀመጫዎች በአደጋ ጊዜ የሚኖረውን ጉዳት የመከሰት ስጋት ከ71-82% ይቀንሳሉ። በተጨማሪም በቅርብ የተደረገ ጥናት ከፍ የሚያደርጉ መቀመጫዎች በፊት ከሚታሰበው በላይ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ እና የጉዳት ስጋትን ከ45% በላይ እንደሚቀንሱ አመላክቷል።
የልጅ የመኪና መቀመጫዎች ለልጆች ደኅንነት ወሳኝ ከመሆናቸው ባሻገር በሕጉ መሠረትም አስገዳጅ ናቸው። በMassachusetts ሕግ መሠረት ከ8 ዓመት በታች የሆኑ ማንኛውም ተሳፋሪ ቁመታቸው ከ57 ኢንቾች በላይ ካልሆነ በስተቀር የልጅ ተሳፋሪ የደኅንነት መቀመጫ ሥርዓት ላይ በአግባቡ መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ይህንን ሕግ መጣስ በፍትሐ ብሔር ክርክሮች ላይ ለአደጋ አስተዋጽዖ ያበረከተ ቸልተኝነት ተደርጎ የማይወሰድ ቢሆንም፣ እስከ $25 የሚደርስ ቅጣት ሊያስከትል ይችላል።
የMassachusetts የልጅ የመኪና መቀመጫ ሕግ ላይ የተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች አሉ። አንድ ልጅ የሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ ከሆነ የመኪና የደኅንነት መቀመጫ ላይ እንዲቀመጥ አይገደድም፦
1. በትምህርት ቤት አውቶቡስ ላይ እየተሳፈረ ከሆነ።
2. ከጁላይ 1፣ 1900 በፊት በተሰራ የደኅንነት ቀበቶ ያልተገጠመለት ሞተር ተሽከርካሪ ውስጥ ከሆነ።
3. በተረጋገጠ የጤና ችግር ምክንያት የተለመደ የተሳፋሪ ደኅንነት መቀመጫ ወይም ልዩ የደኅንነት መቀመጫን መጠቀም የማይችል ከሆነ።
ብዙ ወላጆች እና አሳዳጊዎች የመኪና መቀመጫዎች ዙሪያ ጥያቄዎች ያሏቸው ሲሆን፣ ስህተቶችም የተለመዱ ናቸው። የተወሰኑት በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ ስህተቶች የሚከተሉት ናቸው፦
• ወደኃላ የዞሩ የልጅ የመኪና መቀመጫዎች ላይ መስታወቶችን መጠቀም፦ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ብዙ ጊዜ ልጃቸውን ማየት እንዲችሉ መስታወቶችን የሚያስቀምጡ ሲሆን፣ አደጋ ሲፈጠር ወይም ቢወድቅ አደገኛ ሊሆን ይችላል።
• ትክክል ያልሆነ የLATCH ሥርዓት አጠቃቀም፦ የLATCH (Lower Anchors and Tethers for Children) (ለልጆች ዝቅ የሚሉ መልህቆች እና ከላይ ማሰሪያዎች) ሥርዓት ከላይ እስከታች ድረስ በአግባቡ መታሰር ያለበት ቢሆንም፣ ብዙውን ጊዜ ቀበቶዎቹ ስለሚጠማዘዙ ውጤታማነታቸው ይቀንሳል።
• የላሉ ወይም የተጠላለፉ የደኅንነት ቀበቶዎች፦ የልጅ የደኅንነት ቀበቶ ምንም መጠማዘዝ ወይም መላላት ሳይኖርበት ሰውነትን በአግባቡ የሚይዝ እና ጠፍጣፋ ሆኖ የሚያርፍ መሆን ይኖርበታል።
የCambridge ነዋሪዎች Child Safety Seat Installation (የልጅ የደኅንነት መቀመጫ ገጠማ) ቡድን ጋር ኢሜይል በመላክ ወይም ወደ 617-349-3238 በመደወል የልጅ የመኪና መቀመጫ ፍተሻ ቀጠሮ ማስያዝ ይችላሉ። ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ የልጆች የመኪና መቀመጫዎችን በመፈተሽ ከ25 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው መኮንን David Szeto መቀመጫው የደኅንነት መስፈርቶችን የሚያሟላ እና በአግባቡ የተገጠመ መሆኑን ያረጋግጣሉ። Szeto ከ20 ዓመት አካባቢ በፊት Cape Cod መንገድ ላይ ከመኪናው ኋላ በተፈጠረ ግጭት ወቅት በአግባቡ የተገጠመ የልጅ የመኪና መቀመጫ የአንድን ልጅ ሕይወት ያተረፈበትን ሁኔታ ያስታውሳሉ። አመስጋኙ አባት በኋላ ላይ ላገኙት እርዳታ ያመሰገኗቸው ሲሆን፣ ይህም የልጅ የመኪና መቀመጫ ደኅንነትን ወሳኝነት አጉልቶ አሳይቷል።
ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች የልጅ የመኪና መቀመጫ በሚገዙበት ጊዜ ከሚያጋጥሟቸው ከፍተኛ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ወጪው ነው። የልጅ የመኪና መቀመጫዎች ውድ ሊሆኑ የሚችሉ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ያስወጣሉ። ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች መቀመጫ ሲመርጡ ከበጀታቸው በላይ ወጪ እንዳያወጡ መኮንን William Macedo ይመክራሉ። በገበያ ላይ ያሉት ሁሉም የልጅ የመኪና መቀመጫዎች የደኅንነት መስፈርቶችን የሚያሟሉ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ ተጨማሪ ምቾት እና ተጨማሪ ባህሪያትን ያቀርባሉ።
የልጅ የመኪና መቀመጫ የመግዛት አቅም ለሌላቸው ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች የCambridge Police Department በነፃ የሚቀርብ የልጅ የመኪና መቀመጫ ሊኖረው ይችላል። የልጅ የመኪና መቀመጫ ማግኘት ይችሉ እንደሆነ ለማየት እንዲያነጋግሯቸው Szeto የተቸገሩ ቤተሰቦችን ያበረታታሉ።
እነዚህን ፍተሻዎች የሚያከናውኑት መኮንኖች Safe Kids Worldwide ከተሰኘው ለልጆች ደኅንነት የሚሠራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ልዩ ሥልጠና ያገኛሉ። ባላቸው ሙያ ወላጆች እና አሳዳጊዎች የልጆቻቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስፈልጋቸውን እውቀት ማግኘታቸውን ያረጋግጣሉ።
አግባብ የሆነ የልጅ የመኪና መቀመጫ አገጣጠም በመንገድ ላይ የልጆችን ደኅንነት ለመጠበቅ ወሳኝ ነው። የCambridge Police Department ይህን አስፈላጊ አገልግሎት ለነዋሪዎች በመስጠት እያንዳንዱ ልጅ ደኅንነቱ ተጠብቆ መጓዙን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሠራል። Cambridge ውስጥ የሚኖሩ ወላጅ ወይም ተንከባካቢ ከሆኑ የልጅዎ የመኪና መቀመቻ በአግባቡ የተገጠመ እና የታሰረ መሆኑን ለማረጋገጥ ከዚህ ነፃ ፕሮግራም ተጠቃሚ ይሁኑ።
የልጅ የመኪና መቀመጫ ደኅንነት ዙሪያ የበለጠ መረጃ ለማግኘት የልጅ የመኪና መቀመጫዎች ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎችን ይጎብኙ።