የቤተሰብዎን ያለፈ ታሪክ ይወቁ፦ በCambridge Public Library የሚገኙ የዘር ሐረግ ግብዓቶች
ረቡዕ ፣18 ጁን 2025
"
የቤተ መጻሕፍቱ የዘር ሐረግ አገልግሎቶች ቀላል ሆኖ ጥልቀትም ላለው ዓላማ ይገኛሉ፦ "ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን እንዲያገኙ ለመርዳት። — Drew Griffin፣ አንጋፋ የቤተ መጻሕፍት ባለሙያ
"
ስለ ቤተሰብዎ ታሪክ አስበው ያውቃሉ? የDNA ምርመራ ላይ በታየው እድገት እና የቅድም አያቶችን ማንነት ለማወቅ እየጨመረ በመጣው ጉጉት ምክንያት ከመቼውም ይበልጥ ተጨማሪ ሰዎች የዘር ሐረጋቸውን የመፈለግ ጉዞ እየጀመሩ ነው። ቤተሰብዎ ከCambridge ጋር ትስስር ካለው የCambridge Public Library (የCambridge የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት) ያለፈ ታሪክዎን ማወቅ እና ከእርስዎ በፊት የመጡት ሰዎች ታሪክ ጋር ግንኙነት መፍጠር እንዲችሉ የሚረዱ የተለያዩ የዘር ሐረግ አጋዥ ግብዓቶችን ያቀርባል።
የልደት፣ የጋብቻ ወይም የሞት መዝገቦችን እየፈለጉ ከሆነ፣ የCambridge City Clerk’s Office (የCambridge ከተማ አስተዳደር ጸሐፊ ጽሕፈት ቤት) ጥሩ የመጀመሪያ አማራጭ ነው። ከ1630 ጀምሮ እስከ 1848 ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍኑ መዝገቦችን ይይዛሉ። በተጨማሪም ከ1630-1829 ያሉት የንብረት መዝገቦች ለምርምር ይገኛሉ። ተመራማሪዎች የቤተ ክርስቲያን መዛግብት ከፈለጉ አብዛኛውን ጊዜ እያንዳንዱን ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ ማነጋገር ይችላሉ።
ሆኖም ታሪካዊ የተማሪ መዝገቦችን ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች የተዋሃዱ ወይም አሁን የማይገኙ ሲሆኑ፣ የCambridge Public Libraryም ሁሉን አቀፍ የሆነ የተማሪ መዝገቦች ስብስብ እስካሁን አላገኘም። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ጠቃሚ የቤተሰብ ታሪክ ማግኘት የሚቻልበት ብዙ መንገዶች አሉ።
ቤተ መፃህፍቱ የሚከተሉትን ጨምሮ ተመራማሪዎች የቤተሰብ ታሪካቸውን ማወቅ እንዲችሉ ለሚረዱ በርካታ ቁልፍ የመረጃ ቋቶች ተደራሽነት ያቀርባል፦
• የCambridge ታሪካዊ ጋዜጦች ስብስብ (1846-2015)፦ መጣጥፎች፣ ማስታወቂያዎች እና የሞት ማስታወሻዎችን የያዙ የአካባቢው ጋዜጦችን ያሰባሰበ ሰፊ መዝገብ ቤት።
• የከተማ አስተዳደር የመረጃ ማውጫዎች (1848-1972)፦ እነዚህ በነዋሪዎች፣ የንግድ ሥራዎች፣ የመንግስት ጽሕፈት ቤቶች እና ሲቪል ድርጅቶች ዙሪያ ዝርዝር መረጃ ያቀርባሉ።
• ከ1904 እና ከ1932-1947 ያሉ የመራጭ አስተያየት ዝርዝሮች፦ ወንዶች እና ሴቶችንም የሚያካትቱ የመራጮች ምዝገባ መዝገቦች።
ከእነዚህ አጋዥ ግብዓቶች መካከል አብዛኝውቹ ኦንላይን የሚገኙ በመሆኑ፣ ከየትም ቦታ ሆኖ ምርምር ማከናወን ከመቼውም በላይ ቀላል ሆኗል።
2016 ላይ Drew Griffin እና Alyssa Pacy የተሰኙ አንጋፋ የቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎች በCambridge Public Library አራት ክፍሎች ያሉት የዘር ሐረግ ኮርስ አስጀምረዋል። ተከታታይ ትምህርቱ የሚከተሉትን ሸፍኗል፦
1. የዘር ሐረግ ምርምር መግቢያ
2. ኦንላይን አጋዥ ግብዓቶችን እንዴት በውጤታማነት መጠቀም እንደሚቻል
3. ጥልቅ ምርምር ለማድረግ ውጫዊ ምንጮችን ጥቅም ላይ ማዋል
4. በዘር ሐረግ ውስጥ የDNA ምርመራን ሚና መረዳት
ቤተ መፃህፍቱ የሚከተሉትን ጨምሮ ቁልፍ ለሆኑ የዘር ሐረግ መረጃ ቋቶችም ተደራሽነት ያቀርባል፦
• Ancestry.com
• HeritageQuest
• African American Historical Records
• The Cambridge Chronicle Archives
እንደ Ancestry.com ያሉ አንዳንድ የመረጃ ቋቶች የቤተ መጻሕፍት ካርድ የሚጠይቁ ቢሆንም፣ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ያለ ካርድ ሊገኙ ይችላሉ።
ለዘር ሐረግ ምርምር እጅግ ጠቃሚ ከሚባሉት መሣሪያዎች መካከል አንዱ በየአስር ዓመቱ የሚሻሻለው የU.S. የሕዝብ ቆጠራ ነው። ነገር ግን የተጀመረው በ1790 በመሆኑ ቀደም ያሉ መዝገቦች ላይ ምርምር የሚሠሩ ሰዎች እንደ የንብረት መዝገቦች ወይም የቤተ ክርስቲያን መዝገብ ቤቶች ያሉ አማራጭ ምንጮች ላይ መተማመን ሊኖርባቸው ይችላል።
ሌላው ጠቃሚ ግብዓት ከ1848 ጀምሮ የነበሩትን ነዋሪዎች እና የሥራ ዘርፎቻቸውን የሚዘረዝሩት የCambridge ከተማ አስተዳደር የመረጃ ማውጫዎች ናቸው። በተጨማሪም የCambridge City Clerk’s Office የጋብቻዎች፣ ልደቶች እና ሞቶች ይፋዊ መዝገቦችን የያዘ ሲሆን፣ የቤተሰብ የዘር ሐረግን ለማወቅ ሌላ አማራጭ መንገድ ያቀርባል።
የቤተሰብ ታሪክን መመርመር አስደሳች ቢሆንም፣ በተለይ ለአንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች ግን ተግዳሮቶች ሊኖሩት ይችላሉ፦
• የሴቶች ስም ለውጥ፦ ጋብቻዎች በአብዛኛው የአባት ስም ለውጥ የሚያስከትሉ በመሆኑ ሴቶችን በታሪካዊ መዝገቦች ለመከታተል አስቸጋሪ ያደርገዋል።
• የአፍሪካዊ አሜሪካዊያን የዘር ሐረግ፦ በባርነት የተገዙ ግለሰቦች ብዙውን ጊዜ መደበኛ መዝገቦች ውስጥ የማይካተቱ በመሆናቸው አማራጭ የምርምር ስትራቴጂዎችን ይጠይቃል።
• የአይሁድ የዘር ሐረግ፦ በሆሎኮስት ምክንያት ብዙ መዝገቦች በመጥፋታቸው የዘር ሐረግ ለማወቅ የሚደረገውን ጥረት አወሳስበውታል።
• የጉዲፈቻ መዝገቦች፦ ከ1900 በፊት የነበሩት ጉዲፈቻዎች በብዛት ኢ-መደበኛ እና ያልተመዘገቡ ስለነበሩ ለመከታተል አስቸጋሪ ናቸው።
እነዚህ ተግዳሮቶች እያንዳንዳቸው የተለዩ የምርመራ ዘዴዎችን ይጠይቃሉ። ለምሳሌ የአፍሪካዊ አሜሪካውያን የዘር ሐረግ ዙሪያ በሚሠሩበት ጊዜ ተመራማሪዎች "ከአሁን ጀምረው ወደኃላ እንዲዳስሱ" Alyssa Pacy ይመክራሉ። እንቅፋቶች ሲኖሩ በምርመራ ዘዴዎች ረገድ ፈጣሪነት እንዲኖር እና እንደ የቤተ ክርስቲያን መዝገብ ቤቶች ያሉ አማራጭ መዝገቦች እንዲዳሰሱ ያበረታታሉ።
ብዙ ሰዎች የዘር ሐረግ ምርምር የሚጀምሩት ዝነኛ አያት ቅድም አያቶች ይገኛሉ በሚል ተስፋ ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ ግን ጉዞው ወደ ያልተጠበቁ ግኝቶች ያመራል። ይህ ለአንዳንዶች በፊት ያልታወቀ የአፍሪካዊ አሜሪካዊ ዘር ግኝት ሲሆን፣ ለሌሎች ደግሞ የቤተሰብ ሚስጥሮች መገለጥ ሊሆን ይችላል።
የቤተ መጻሕፍት ባለሙያዎች የሆኑት Pacy እና Griffin የዘር ሐረግ የተፈለጉም ሆነ ያልተፈለጉ አስደናቂ ነገሮችን ሊያስከትል እንደሚችል ተመራማሪዎችን ሁሌም ያስታውሳሉ። ለምሳሌ አንድ ደንበኛ አያታቸው አጭበርባሪ ነገር ነበሩ የሚል ለረጅም ጊዜ የቆየን ጥርጣሬ በጋዜጣ መዝገቦች አማካኝነት ማረጋገጥ ችለዋል። እንደ እድል ሆኖ ግን ጉዳዩን በተጫዋጭነት ማየት ችለው የቤተሰባቸውን ታሪክ ማረጋገጥ በመቻላቸው አመስጋኝ ሆነዋል።
በአሁኑ ወቅት የCambridge Public Library መርሃ ግብር የያዘላቸው ምንም ዓይነት የዘር ሐረግ ወርክሾፖች ወይም ዝግጅቶች የሌሉት ቢሆንም፣ ተጨማሪ የማወቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ግን የወደፊት ፕሮግራሞች ዙሪያ አዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የቤተ መጻሕፍቱን ወርሃዊ የዜና መጽሔት ማየት ይችላሉ።
Drew Griffin እንደገለጹት፣ የቤተ መጻሕፍቱ የዘር ሐረግ አገልግሎቶች ቀላል ሆኖ ጥልቀትም ላለው ዓላማ ይገኛሉ፦ "ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን እንዲያገኙ ለመርዳት።" ብዙ አሜሪካውያን የዘር ሐረግ ምርመራ ማድረግ የሚጀምሩበትን ምክንያት ሲጠቅሱ እንደተናገሩት "አሜሪካውያን እንደመሆናችን መጠን ከየት መጣን የሚለውን ሁሌም ላናውቅ እንችላለን።" United States በስደተኞች የተገነባች ሀገር በመሆኗ የራስን የዘር ሐረግ ማወቅ የግል ታሪክን ለመረዳት ወሳኝ እርምጃ ሊሆን ይችላል።
ምርምርዎን ገና እየጀመሩ ወይም አያት ቅድም አያቶችዎ ዙሪያ ጠለቅ ያሉ ግንዛቤዎችን ለማግኘት እየሞከሩ ቢሆንም፣ የCambridge Public Library የቤተሰብዎን ታሪክ ለመግለጥ ወሳኝ ግብዓት ነው። ወደ ያለፈው ዘመን ጉዞዎን ለመጀመር ዛሬውኑ ቤተ መጻሕፍቱን ይጎብኙ ወይም ኦንላይን ግብዓቶቹን ይዳስሱ።