በCambridge’s Rodent Control ፕሮግራም የአይጥ ችግሮችን ይከላከሉ
ረቡዕ ፣18 ጁን 2025
Cambridge Inspectional Services Department (የCambridge የፍተሻ አገልግሎቶች መምሪያ) በመኖሪያነት ለሚያገለግሉ ንብረቶች የቤት ውጪ አገልግሎቶችን በነፃ እያቀረበ ነው። የከተማ አስተዳደሩ የአይጥ ችግሮችን ለመከላከል እንዲረዳ Private Property Rodent Control ፕሮግራም ላይ እንዲሳተፉ ነዋሪዎችን በማበረታታት ላይ ይገኛል።
በ2021 የተጀመረው ይህ ፕሮግራም ከ900 በላይ ለሚሆኑ ብቁ ንብረቶች የአይጥ መቆጣጠሪያ አገልግሎቶችን አቅርቧል። እንዲሁም የአካባቢ ጤና ፕሮጀክት አስተባባሪ David Power እንደገለጹት፣ ተቆጣጣሪዎቹ አይጥ መከላከያ ዘዴዎች ዙሪያ ለነዋሪዎች ትምህርት ይሰጣሉ። በኮንትራት የተያዙ፣ ፈቃድ ያላቸው እና ኢንሹራንስ የያዙ ኩባንያዎች ጋር በመሥራት እና የባለሙያ ሪፖርቶች እና ክትትሎችን በመጠቀም የተባይ ቁጥጥር ኩባንያው የሚጠበቅበትን ነገር የሚያሟላ መሆኑን ያረጋግጣሉ።
Power በሂደቱ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ መሠረት፣ አንድ ማመልከቻ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ መጀመሪያ የስጋት ግምገማ የሚያከናውኑ የከተማ አስተዳደር ተቆጣጣሪ ጉብኝት ያደርጋሉ። ከዚያም ከአንድ እስከ ሁለት ሳምንታት በኋላ አመልካቹ የመጀመሪያ አገልግሎት ቀጠሮ እንዲይዙ የሥራ ተቋራጭ የሚያነጋግራቸው ሲሆን፣ እሱም ንብረቱን ይገመግም እና ማናቸውም የአይጥ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ መፍትሄ ያቀርባል። ከዚህ በኋላ ሶስት የክትትል ጉብኝቶች የሚኖሩ ሲሆን፣ የመጨረሻው ጉብኝት ላይ ሥራ ተቋራጩ ለአይጥ ቁጥጥር የተቀጠውን መሣሪያ ካስወገደ በኋላ የከተማ አስተዳደር ተቆጣጣሪው ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ንብረቱን ይገመግማሉ።
አይጦችን ለመከላከል ዋነኛው መፍትሔ የንፅሕና አጠባበቅ ሲሆን፣ Power "ሁሉም ሰው ቆሻሻውን እና ግቢውን መንከባከብ ይኖርበታል" ሲሉ ተናግረዋል። "በመኖሪያ ሰፈሩ ውስጥ የሚገኝ አንድ ቸልተኛ በርካታ ያልተፈለጉ ተባዮችን ሊስብ ይችላል። የመንገድ ዳር ቆሻሻን መቆጣጠር እና ምግብን ከቦታው ማራቅ ሁሉም ሰው በመኖሪያ ሰፈሩ የሚገኙ ንብረቶች ከአይጥ ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ የሚችልባቸው መንገዶች ናቸው።"
እስካሁን ፕሮግራሙን የማስፋፋት ዕቅዶች ባይኖሩም፣ ቡድኑ ግን እንደ በየወሩ ወይም በወር ሁለቴ የሚላኩ ኢሜይሎች ወይም ልጥፎች ያሉ ነገሮችን በመጠቀም ተጨማሪ ሰዎችን እያስተማረ ይበልጥ አጠቃላይ የሆነ ግንዛቤ ማስጨበጫ መሥራት እንደሚፈልግ Power ይናገራሉ። እንዲሁም ከአንድ ዓመት በኋላ ተመልሰው ነዋሪዎችን የሚጎበኙበት የረጅም ጊዜ ግብረመልስ ዕቅድ ተግባራዊ የማድረግ ሃሳብም አላቸው።
ነዋሪዎች አይጦችን ለመከላከል የሚወሰዱት እርምጃዎች ዙሪያ የበለጠ ለማወቅ ተነሳሽነት መያዛቸውም አስፈላጊ ነው። የመጀመሪያው እርምጃ አይጦች በሚኖሩባቸው እንደ የአይጥ ጎጆዎች ወይም ጎሬዎች ያሉ ቦታዎች ላይ ማስረጃዎችን መፈለግ ነው። ዓይነ ምድር እና ጉድጓዶችን እንዲሁም በእንጨት ወይም በፕላስቲክ የተሰሩ የቆሻሻ በርቤሎች ላይ ያሉ የመታኘክ ምልክቶችን ይፈልጉ። ግድግዳዎች እና ሳር ላይ የአይጥ መተላለፊያ መንገድ ምልክቶች መኖራቸውን ይፈትሹ።
አይጦች በሽንት እና በዓይነ ምድራቸው አማካኝነት እርስ በእርስ መልዕክት ስለሚያስተላልፉ እና ስለሚጠራሩ ሁለተኛው እርምጃ ዓይነ ምድር እና የአይጥ መተላለፊያ መንገድ ምልክቶችን ማጽዳት ይሆናል። ኮተት ማስወገድ አይጦች የሚደበቁበት፣ የሚተኙነት፣ ጎጆ የሚሠሩበት እና የሚራቡበትን ቦታ ያሳጣል። በተጨማሪም አረሞችን፣ ቁጥቋጦዎችን እና አጫጭር አትክልቶችን መቆጣጠር ወሳኝ ነው።
ሶስተኛው እርምጃ ቆሻሻዎን በአግባቡ በመያዝ እና ሁሉንም ምግብ በማራቅ አይጦቹን ማስራብ ነው።
አራተኛው እርምጃ በመሠረት፣ ግድግዳ፣ ወለሎች፣ በሮች ሥር እና መስኮቶች ዙሪያ ያሉትን ቀዳዳዎች ወይም ስንጥቆች በመድፈን መግቢያ እንዲያጡ ማድረግ ነው። አምስተኛው እርምጃ ወጥመድ በመጠቀም አይጦቹን መጨረስ ሲሆን፣ መርዞቹ ግን ሙያው ባላቸው የተባይ ቁጥጥር ኩባንያዎች ብቻ መደረግ ይኖርባቸዋል።
ለሁሉም ሰው አይጥ መከላከል የሚቻልበት ምርጡ መንገድ እንደ ማኅበረሰብ በአንድ ላይ መሥራት ነው። በመኖሪያ ሰፈሩ ውስጥ የሚገኙት ሁሉም ሰዎች ቆሻሻቸውን በመንከባከብ እና የጽዳት ሥራ በመሥራት የድርሻቸውን መወጣታቸውን ማረጋገጥ ወደ መኖሪያ ቤቶች እና ወደ ሰፈሩ ሊሳቡ የሚችሉ አይጦችን ይከላከላል።
"
በመኖሪያ ሰፈሩ ውስጥ የሚገኝ አንድ ቸልተኛ በርካታ ያልተፈለጉ ተባዮችን ሊስብ ይችላል — አይጥ መከላከል ዙሪያ ሁሉም ሰው ሚና ይጫወታል። – David Power፣ የአካባቢ ጤና ፕሮጀክት አስተባባሪ
"