ሴፕቴምበር ወር ረፋድ ላይ በዋለችው ደማቅ ዕለት የCambridge አዲስ የTobin Montessori and Darby Vassall ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና የማኅብረሰብ አገልግሎት ማዕከላት በሮች ለተማሪዎች፣ ለቤተሰቦች እና ለመምህራን ተከፈቱ፤ ይሁንና ይህ ክስተት አዲስ ሕንጻ ከመክፈት ባሻገር እጅግ የላቀ ትርጉም ያለው ክስተት ነበር። ከዐሥርት ዓመታት በላይ የፈጁ የእቅድ፣ የትብብር እና የኢንቨስትመንት ሥራዎች ፍጻሜ ያስገኙት ውጤት ነበር። ይህ ክስተት የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ በልዩ ትኩረት፣ ለእነሱ በሚስማማ መልኩ በተሠሩት የማዕከላቱ የፊት ለፊት በሮች በክብር የገባበት ቅጽበት ነበር።
ለዓመታት የDarby Vassall Upper School ሠራተኞች፣ መምህራን እና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ፈጽሞ ለእነሱ በማይስማሙ ቦታዎች ውስጥ ለመጠቀም ተገድደው ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የTobin Montessori ተማሪዎች የምግብ አዳራሽ ወይም ተለቅ ያለ መጫወቻ ስፍራ አልነበራቸውም። ተማሪዎች እና መምህራን ለመማሪያ ባልተሠሩ እንዲሁም በግድ ወደ መማሪያ ቦታነት በተለወጡ ክፍሎች ውስጥ ተጨናንቀው ሲማሩ፣ የሳይንስ ላቦራቶሪ ሥራዎችን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሲያከናውኑ፣ ጂምናዚየሞችን በጋራ ሲገለገሉ፣ ቢሮዎችንም የሆኑ ጥጎች ላይ ተወሽቀው ሲገለገሉ ቆይተዋል።
የDarby Vassall Upper School ርዕሰ መምህር Daniel Coplon-Newfield «በትምህርት ቤታችን ታሪክ የራሳችን የፊት ለፊት ዋና በር ፈጽሞ ኖርዎን አያውቅም» ብለዋል። «ከTobin Montessori School እና ከሌሎች ውድ ወዳጆቻችን ጋር ቦታዎቹን ስንጋራ ስለቆየን፣ ሁልጊዜ ተከራዮች እንደሆንን ነበር የሚሰማን፣ የመንገድ ምልክቶቻችን ጊዜያዊ፣ የመኖራችን ጉዳይ ጽኑ አይመስለንም ነበር።»
ዛሬ ተከራይ እንደሆንን የሚሰማን የነበረው ስሜትም ምሳሌም ጠፍቷል። የ359,100 ስኩዌር ጫማ ስፋት ያለው፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘው አዲስ ሕንጻ፣ የTobin Montessori School (316 ተማሪዎች፣ ከአጸደ ሕፃናት ፕሪ-ኬ እስከ 5ኛ ክፍል)፣ የDarby Vassall Upper School (DVUS) (300 ተማሪዎች፣ 6ኛ እስከ 8ኛ ክፍል)፣ የCPS Special Start እና DHSP Preschool Programs (80+ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ተማሪዎች)፣ የDHSP Community School Afterschool Program (100 ተማሪዎች)፣ የአትሌቲክስ መገልገያዎችን፣ የሥነ ጥበብ ማሳያ ስፍራዎችን፣ መጫወቻ ሜዳዎችን እና የማኅበረሰብ መገልገያዎችን የያዘ የማኅበረሰቡ ማማ በመሆኑ፣ ለዛሬዎቹ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሚመጡት ትውልዶችም ጭምር የCambridge ከተማ አስተዳደር እና Cambridge Public School District በከተማዋ የወደፊት ሁኔታ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸውን የማይወላውል ቁርጠኝነት ማሳያ ነው።
«ይህ የሥራ ቁርጠኝነት መኖሩን ያሳያል» ሲሉ ርዕሰ መምህር Coplon-Newfield ቀጠሉ። «የሲቪክ ማኅበረሰቡን ለማገልገል ብቻ ሳይሆን፣ ለትምህርትም ቁርጠኝነት መኖሩን ያሳያል። ይህ ሌሎች ከተማዎች የሚያደርጉት ዓይነት ኢንቨስትመንት አይመስለኝም። ይህ በትምህርት ሥርዓታችን እና በማኅበረሰባችን ላይ የተደረገ ኢንቨስትመንት ውጤት ሲሆን፣ በእርግጥም ልንኮራበት የሚገባ እና አቅልለን ማየት የሌለብን ሥራ ነው።»
ሕዝባዊ መሠረት
በአንድ ወቅት በWest Cambridge በሚገኘው Vassal Lane፣ Concord Avenue እና Alpine Street አጠገብ ይገኝ የነበረውን የብሩታሊስት ዘመን ሕንጻ በመተካት፣ አዲሱ ተቋም ከመላው Cambridge የመጡ 1,000 የሚጠጉ ሕጻናትን ያገለግላል።
የከተማ አስተዳደሩ ንድፍ ሲያወጣ ቦታው ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ በማሰብ ነው። በተጨማሪም 400 መቀመጫዎች ያለው የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ሁለት መደበኛ መጠን ያላቸው ጂምናዚየሞች፣ የአትሌቲክስ ሜዳዎች፣ መጫወቻ ስፍራዎች እና ከስድስት ኤከር በላይ የሆነ የሕዝብ አረንጓዴ ስፍራ ያለው የማኅበረሰብ ማዕከል ነው። የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች ግቢውን ከከተማዋ ሰፊ አውታር ጋር በማገናኘት፣ ባሌቤትነቱ የሁሉም ሰው የሆነ ሕዝባዊ ምልክት ስፍራ እንዲሆን ያደርገዋል።
የCapital Building Projects ዳይሬክተር እና የአዲሱ ግቢ የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት Brendon Roy «ይህ ከትምህርት ቤት ሕንጻ በላይ ነው» ብለዋል። «ይህ የማኅበረሰብ ማዕከል ነው። ትምህርት፣ መዝናኛ፣ ሥነ ጥበባት እና ማኅበራዊ ሕይወት በአንድ ላይ የሚሰባሰቡበት ስፍራ ነው።»
ኦቲዝም ላለባቸው ተማሪዎች የሚስማማውን የመጫወቻ ስፍራ ጨምሮ አራት የተለያዩ መጫወቻ ስፍራዎች በሁሉም የዕድሜ ክልልና ችሎታ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ክፍት ተደርገዋል። በአልማዝ ቅርጽ የተሠሩ ሜዳዎች፣ ክፍት፣ ለብዙ አገልግሎት የሚውል ሜዳ እና የውኃ መርጫ ስፍራዎቹ የግቢውን የውጭ ክፍል ዋና ትኩረት የሚስበው ስፍራ ያደርጉታል። በሕጻው ውስጥ የሚገኙት ሁለት ጂምናዚየሞች እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘው የስብሰባ አዳራሽ ተማሪዎችም ሆኑ የማኅበረሰቡ አባላት መሰብሰብ፣ ዝግጅት ማቅረብ እና መጫወት እንዲችሉ ያደርጋሉ።
የሕዝብ ጥበብ ሥራዎች እና ማኅበረሰቡን ያገናዘቡ የንድፍ ምርጫዎች ሕንጻው ሳይነጠል የሰፈሩ አካል መሆን መቻሉን ያረጋግጣሉ። የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች፣ አዳዲስ መንገዶች እና አረንጓዴ መሠረተ ልማቶች ትምህርት ቤቱን ከWest Cambridge ጋር ያለምንም ክፍተት ያገናኙታል።
በዓላማ የተነደፈ
እያንዳንዱ የሕንጻው ገጽታ የተማሪዎችን ልዩ የእድገት ፍላጎቶች ለማገልገል ያለመ የዓመታት ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ አተገባበርን ያንጸባርቃል። ንድፉ ነጻነትን እና ድጋፍን የሚያመጣጥሙ ቦታዎችን በመፍጠር፣ ለዕድሜ ተስማሚ የሆነ የትምህርት ሥርዓትን ያበረታታል። የመካከለኛ ደረጃ ተማሪዎች በጋራ የማስተማር ሥርዓት እንዲኖር የሚያበረታቱ ተለማጭ የትምህርት ክፍሎች እና የቦታ መጨናነቅን የሚቀንሱ ሰፋፊ ኮሪደሮች በማግኘታቸው የሚጠቀሙ ሲሆን፣ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ደግሞ የMontessori መርሆዎችን በሚያከብሩ አካባቢዎች ውስጥ መማር ይችላሉ።
የTobin Montesorri ርዕሰ መምህር Jaime Frost «በንድፍ ሂደት ውስጥ ባሉት እያንዳንዱ ደረጃዎች በመሳተፋችን ምክንያት የመምህራንና የተማሪዎቻችንን ፍላጎቶች ብቻ ሳይሆን፣ ልጆች የሚማሩበትን መንገድ የሚቀይሩ እንዲሁም በተሻለ ሁኔታ ልንደግፋቸው የምንችላቸውን አካላትም ማካተት ችለናል።» ብለዋል።
በሕንጻው ውስጥ ማዕከላዊው «የትምህርት ቤቱ ልብ» የተሰኘው ቦታ ትስስር እና ትብብርን በማበረታታት እንደ መገናኛ ሆኖ ያገለግላል።
Wayfinding (መንገድ ማፈላለጊያ) በCambridge የራሱ የተፈጥሮ ታሪክ የተነሳሳ ነው። እያንዳንዱ የሕንጻው ክፍል አራቱን ንጥረ ነገሮች (ምድር፣ አየር፣ እሳት እና ውኃ) እና የቦታውን ሥነ-ምህዳር ክልሎች ምሳሌ በማድረግ፣ ልጆች ከቦታው ጋር ቁርኝት እንዲመሠርቱ ይረዳል። የባዮፊሊክ ዲዛይን ዘይቤዎች፣ የተትረፈረፈ የቀን ብርሃን እና የተሻሻሉ የውጭ እይታዎች ጤንነትን የሚደግፉ ሲሆኑ፣ ተማሪዎችም ሕንጻውን እንደ ሕያው የማስተማሪያ መሣሪያ እንዲመለከቱት ይጋብዛሉ።
የውጪው ከጡብና ከብረት የተሠራው ክፍል የሸክላ ማውጫ ቦታ የነበረውን የቦታውን ታሪክ ያከበረ ሲሆን፣ አጠቃላይ «በፓርክ ውስጥ ያለ ትምህርት ቤት» የሚለው ራዕይ ደግሞ ሕዝባዊ ማንነትን ከተፈጥሯዊ አካባቢዎች ጋር ያዋህዳል።
የወደፊት ኢንቨስትመንት
በዋናነት ይህ ፕሮጀክት Cambridge ለዘላቂ ልማት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳያል። በከተማዋ Net Zero Action Plan (ኔት ዜሮ የድርጊት ዕቅድ) መሠረት ለኔት ዜሮ ልቀቶች ታስቦ የተነደፈ በመሆኑ፣ በCambridge ውስጥ በጣም ኃይል ቆጣቢ የሆነ የትምህርት ቤት ሕንጻ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የመሬትና የአየር ሙቀት አማቂ ፓምፖች ሙቀት እና ቅዝቃዜ የሚሰጡ ሲሆን፣ በፀሐይ ብርሃን ኅይል ለማመንጨት የሚያስችለው ጣሪያ ደግሞ በዓመት ወደ 1.1 ሚሊዮን ኪሎ ዋት በሰዓት (kWh) ኅይል በማመንጨት የሕንጻውን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ያካክሳል።
ከመሬት በታች ያለው የመኪና ማቆሚያ መሠረተ ልማት 100% የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ መሙላትን መደገፍ የሚችል ሲሆን፣ የቦታው ላይኛው ክፍል ከመኪና ነጻ በመሆኑም ቦታው ላይ ዛፎች፣ ሜዳዎችና እግረኛ መንገዶች እንዲኖሩ የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል። እስከ 2035 ዓ.ም ድረስ ግቢው በከተማ አስተዳደሩ ደንቦች ላይ የተቀመጠውን ግብ አልፎ የዛፍ ሽፋኑን በሦስት እጥፍ የሚያሳድግ ሲሆን፣ ይህም ተፈጥሯዊ አየር የሚተነፍስ ትምህርት ቤት የሚለውን ራዕይ ያጠናክራል።
ከዚህ በተጨማሪ ቦታው የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም ምሳሌም ሆኗል። ከፍ ያለ የቦታ ደረጃ የመሬት ወለሉን ለ2070 ዓ.ም ከተገመቱ የጎርፍ መጠን ትንበያዎች በላይ ከፍ አድርጎ የሠራ ሲሆን፣ 1.25 ሚሊዮን ጋሎን የሚይዘው ከመሬት በታች ያለው ማጠራቀሚያ፣ የዝናብ አትክልቶች እና ባዮስዌልስ የዝናብ ውኃን በመያዝ ለአትሌቲክስ ሜዳዎች ውኃ ማጠጣትን ጨምሮ እንደገና ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ያስችላሉ።
የቁሳቁስ ጤናማነትም ዋነኛ ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ ነበር፦ የተመረጡት እያንዳንዱ ቁሳቁሶች ከ«ቀይ ዝርዝር» ኬሚካሎች ነጻ የመሆን የLiving Building Challengeን ጥብቅ መስፈርቶች ያሟሉ ናቸው። የቤት ውስጥ የአየር ጥራት ንቁ ክትትል የሚደረግበት ሲሆን፣ የሚከፈቱ መስኮቶች ኃይልን እና ጤንነትን ለመጠበቅ ከሜካኒካል ሥርዓት ጋር የተገናኙ ናቸው።
እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ለተቋሙ የLEED Platinum certification (ሊድ ፕላቲነም ማረጋገጫን) በማስገኘት፣ ለዘላቂ የሕዝብ ሥነ ሕንጻ አዲስ ምሳሌ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
«አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የሚገነቡ ብዙ ማዘጋጃ ቤቶች አሉ» ሲሉ Roy ተናግረዋል። «ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ወደፊት ለሚመጡ ተማሪዎች በቂ ቦታ የያዘ፣ ዘላቂነት እና መቋቋምን ግንባር ቀደም ያረገ፣ በትምህርት እና በማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን ኩራት የሚያንጸባርቅ ዲዛይን ለመንደፍ ጽኑ ውሳኔ የታየበት ኢንቨስትመንት ግን የሚያደርጉ ጥቂቶች ናቸው።»
አዲስ ማንነት እና የባለቤትነት ስሜት ያለበት ቦታ
የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብም ራሱን እንደገና ለመግለጽ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሟል። በወቅቱ Vassall Upper School ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት የነበሩ ተማሪዎች አዲስ ስም የመምረጥ ሂደቱን በመምራት፣ በሮቹ ሲከፈቱ አዲስ ሕንጻ ብቻ ሳይሆን፣ የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ መሆኑንም አረጋግጠዋል። ዋና በር፣ አዲስ ስም፣ ለዓላማው በዓላማ የተገነባ ቤት፤ በጋራ የባለቤትነት እና የኩራት ምሳሌያዊ መሠረት ፈጥረዋል።
ይህንን ቦታ በየቀኑ ለሚጠቀሙት ተማሪዎች፣ መምህራን እና ቤተሰቦች ሕንጻው ከሚሰጠው ተጨባጭ ግልጋሎት እኩል ምሳሌያዊ ትርጉሙም አስፈላጊ ነው።
«ይህ ሕንጻ ማንነት ይሰጠናል» ሲሉ ርዕሰ መምህር Coplon-Newfield ተናግረዋል። «ስም፣ ዋና በር እንዲሁም ማኅበረሰባችን የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው የሚያደርግ ቦታ ይሰጠናል። ለዓመታት ጊዜያዊ እንደሆንን ይሰማን ነበር፤ አሁን ግን ቋሚ እንደሆን ነው የሚሰማን። ይህ ደግሞ ሁሉንም ነገር ይለውጣል።»
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ፣ሕንጻው አንድ ከተማ በድፍረት ኢንቨስት ለማድረግ ስትመርጥ ምን ማድረግ እንደሚቻል ለCambridge ማኅበረሰብ ማስታወሻ ነው።
ምስጋና እና ራዕይ
የትምህርት ክፍሎችን ለመቀየር ቁሳቁሶችን እያጓጓዙና እያሰናዱ፣ በተዋሱ የትምህርት ክፍሎች ጥጎች ላይ እያስተማሩና እየተማሩ፣ በየጊዜው መላ እየፈለጉ የሽግግር ዓመታቱን ላሳለፉት ሁሉ ሕንጻው ተመርቆ መከፈቱ ጥልቅ ስሜት ያዘለ ነበር። ይህ የአዲሱ የትምህርት ዓመት መጀመሪያ ብቻ ሳይሆን፣ በCambridge ታሪክ ውስጥ የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ ነው።
የCambridge City Manager የሆኑትም Yi-An Huang «ይህ ፕሮጀክት የብዙዎቹ እሴቶቻችን መግለጫ ነው» ብለዋል። «በትምህርት፣ በዘላቂ ልማት፣ የመቋቋም አቅም በመገንባት እና በማኅበረሰብ እንደምናምን ይናገራል። በCambridge ወደፊት እንደምናምን ይናገራል።»
እናም በዚህ የፎል (መኸር) ወቅት ማለዳ፣ ተማሪዎች በብርሃን በተሞሉት የትምህርት ክፍሎች፣ ከፍታን በተጎናጸፉት ጂምናዚየሞች እና በሰፋፊ መጫወቻ ሜዳዎቹ ላይ ዓይናቸውን በአግራሞት እየጣሉ በሮቹን አልፈው ሲገቡ፣ ያ ወደፊት የሚመጣው መልካም ጊዜ እውን የሚሆንበት አጋጣሚ የሰመረ ይመስላል።