በዚህ ዓመት መጀመሪያ በአንዲት ቀዝቃዛ ቀን ጠዋት ላይ በKendall Square ከአካፋዎች ላይ አፈር ወደ አየር ሲወረወር ይታይ የነበረ ሲሆን፣ የከተማው አስተዳደር ባለሥልጣናት፣ የማኅበረሰብ አጋሮች እና የEversource ተወካዮች መሠረት የጣሉባትን እና ታሪክ የሠሩባትን ቀን ለማክበር ተሰብስበውም ነበር። ከጩኸቶች እና ንግግሮች ባሻገር፣ በU.S. ውስጥ ከዚህ በፊት ከተገነቡት ነገሮች ሁሉ የተለየ የሆነ የፕሮጀክት ጅማሮ ነበር፦ Greater Cambridge Energy Program (GCEP፣ የታላቁ Cambridge የኃይል ፕሮግራም)፣ በአካባቢው የኃይል የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ የተደረገ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ነበር፤ ይህ ሁሉ ነገር ከመሬት በታች እየተከናወነ ነበር።
በአንድ ወቅት የመኪና ማቆሚያ ጋራዥ የነበረበት ቦታ ሲሆን፣ በቅርቡ አረንጓዴ ቦታ፣ ዘመናዊ የላብራቶሪ ሕንጻዎች እንዲሁም ከመሬት በታች 105 feet (ጫማ) ተደብቆ የአገሪቱ ትልቅ ከመሬት በታች የሚገኝ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ይገኛል። ይህ 35,000 square feet (ካሬ ጫማ) ስፋት ያለው ተቋም፣ ለነዋሪዎች እና ለንግድ ድርጅቶች የዕለት ተዕለት ሕይወት በጸጥታ ኃይል እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ከመሬት በላይ ያለውን ቦታ ነጻ በማድረግ ማኅበረሰቡን ያገለግላል።
አዲሱ ከመሬት በታች ያለው ማከፋፈያ ጣቢያ በስምንት አዳዲስ ከመሬት በታች ባሉ የማስተላለፊያ መስመሮች የተገናኘ ሲሆን፣ እነዚህም በአካባቢው ከሚገኙ ነባር ማከፋፈያ ጣቢያዎች ጋር የሚያያዙ ይሆናል። ፕሮጀክቱ የሥርዓት አስተማማኝነትን የሚያጠናክር ሲሆን፣ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት የሚያሟላ እንዲሁም የንጹሕ ኃይል ሀብቶችን ለመጠቀም ሁኔታዎችን ያመቻቻል ተብሎ ይጠበቃል።
የEversource ዋና ሥራ አስፈጻሚ Joe Nolan በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደሚከተለው ብለዋል፦ «ይህ ዘላቂ ልማትን እና ችግር የመቋቋም አቅምን የሚያሻሽል የኃይል የወደፊት ዕጣ ፈንታን የሚቀርጽ የፈጠራ መፍትሔ ነው።» «ከCambridge እና ከአጋሮቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን በመሥራት፣ የዛሬን ፍላጎቶች እያሟላን ለነገው ንጹሕ የኃይል ሽግግር እየተዘጋጀን እንገኛለን።»
ለምን አስፈለገ
ከተማዋ ከቅሪተ አካል ነዳጆች በመራቅ፣ ብዙ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ሙቀት ፓምፖችን እየጫኑ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እየገዙ እና በመንገዳችን ላይ እየነዱ እንዲሁም ሕንጻዎች ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ እየተገነቡ ይገኛሉ። ይህ እድገት ፈተና ይዞ የሚመጣ ሲሆን፣ የኃይል ማስተላለፊያ መረቡ አብሮ ማደግ እንዲሁም ጥገና ማግኘት ይኖርበታል።
GCEP ያንን ለማድረግ ታስቦ የተነደፈ ነው። የመሬት ውስጥ ማከፋፈያ ጣቢያው ሥራ ከጀመረ በኋላ በCambridge ውስጥ ያሉትን ሁሉንም የመኖሪያ ቤቶች ማሞቂያ ለማንቀሳቀስ እና የንግድ ዘርፉን የጋዝ ፍላጎት እስከ ግማሽ በንጹሕ የኤሌክትሪክ ሥርዓቶች ለመተካት በቂ አቅም ይኖረዋል። እንዲሁም ለተጨማሪ ታዳሽ ኃይል ቦታ ያመቻቻል።
የCambridge City Manager Yi-An Huang እንዳሉት፦ «ይህ ፕሮጀክት ስለ አስተማማኝነትን፣ የመቋቋም አቅምን እና ኃላፊነትን ስለመገንባት ነው።» «ማኅበረሰባችን እያደገ ሲሄድ፣ የኃይል ሥርዓቱ ከእኛ ጋር ያድጋል፤ ይህም ከካርበን ነጻ የመሆን ግቦቻችንን በሚደግፍ መልኩ ይሆናል።»
በዓይነቱ የመጀመሪያው የሆነው ዲዛይን
ማከፋፈያ ጣቢያውን ከመሬት በላይ ከመገንባት ይልቅ፣ በBroadway እና በBinney Street መካከል ባለው አዲስ አረንጓዴ ቦታ ስር ተደብቆ ከመሬት በታች እንዲገነባ ተደርጓል። ከላይ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ጎብኚዎች አስደሳች በሆነው መናፈሻ እና ዘመናዊ የሳይንስ ተቋማት መዝናናት ይችላሉ። ከታች ደግሞ የወደፊት የብርሃን፣ ሙቀት እና ቴክኖሎጂ ምንጭ የሆነው ጣቢያ በኃይል የሚንቀሳቀስ ይሆናል።
የCambridge Redevelopment Authority (CRA፣ የCambridge መልሶ ማልማት ባለሥልጣን) ዋና ዳይሬክተር Tom Evans እንዳሉት፦ «CRA እና የCambridge ከተማ አስተዳደር አንድ ላይ በመሆን ለእቅድ አወጣጥ ፈታኝ የሆነውን ሥራ ወደ መልካም አጋጣሚ ለውጠውታል።» «በአንድ ወቅት የመኪና ማቆሚያ ጋራዥ የነበረው ቦታ፣ ወሳኝ የኃይል ማመንጫ ማዕከል፣ ሰዎች አዳዲስ ነገሮችን መማርና ማግኘት የሚችሉበት ስፍራ እንዲሁም ለማኅበረሰቡ ተስማሚ የሆነ ቦታ ይሆናል።»
ከCambridge ባሻገር
ማከፋፈያ ጣቢያው የእንቆቅልሹ አንድ ቁራጭ ብቻ ነው። GCEP በCambridge፣ Somerville እና Boston ውስጥ 8.3 miles (ማይሎች) ርቀት የሚሸፍኑ ስምንት አዳዲስ ከመሬት በታች ያሉ የማስተላለፊያ መስመሮችን፣ በአምስት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎችን እና ወደ 50 የሚጠጉ አዳዲስ የማከፋፈያ መስመሮችን ያካትታል። በአንድነት ይህ የኤሌክቲሪክ መረብ ኃይል በጣም ወደሚያስፈልግባቸው ቦታዎች ለአንድ ቤተሰብ አዲስ የኤልክቲሪክ ቻርጀርም ሆነ፣ ባዮቴክ ላብራቶሪ ውስጥ ላለ የአየር ንብረት መቆጣጠሪያ ሥርዓት ወይም ደግሞ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ ለመኖር ታስቦ ለተነደፈ አዲስ አፓርታማ ሕንጻ ቢሆንም ኤሌክትሪክ በአስተማማኝ ሁኔታ መፍሰስ እንደሚችል ያረጋግጣል።
ወደፊት በማሰብ መገንባት
ፕሮጀክቱ በደረጃዎች ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች እስከ 2029 ዓ.ም ተጠናቅቀው፣ እስከ 2031 ዓ.ም ደግሞ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅ ይሆናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ወደ 500 የሚጠጉ የሙሉ ጊዜ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥር ሲሆን፣ ወደ Kendall Square ቋሚ እንቅስቃሴን እና ብሩህ ተስፋን ያመጣል።
ለCambridge ነዋሪዎች ጥቅሙ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ይንጸባረቃል፦ አውሎ ንፋስ ሲኖር መብራቶች በርተው እንዲቆዩ የሚያረግ፣ ንጹሕ ቴክኖሎጂዎችን የሚደግፍ እና ከተማዋ ከቅሪተ አካል ነዳጆች የበለጠ እንድትርቅ የሚያግዝ ይበልጥ አስተማማኝ የኃይል ሥርዓት ይኖራቸዋል።
የBXP ተወካይ Bryan Koop እንዳሉት፦ «GCEP ስለ ገመዶች እና ትራንስፎርመሮች ብቻ አይደለም።» «ለሰዎች፣ ለሳይንስ እና ለማኅበረሰብ ቦታ በሚፈጥር መልኩ የCambridgeን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ስለማድመቅም ነው።»
መሠረት የተጣሉባቸው አካፋዎች ወደ ጎን ሲቀመጡ እና ሕዝቡ ሲበተን፣ የፕሮጀክቱ ስፋት እና የተገባው ቃል በቦታው ቀረቷል። ወደፊቱ ያለው ሥራ ውስብስብ እና ዓመታትን የሚወስድ ቢሆንም፣ የሚያሳድረው ተጽዕኖው ግን ከKendall Square ያልፋል። ለCambridge የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚሆነው ንጹሕ እና አስተማማኝ የኃይል ምንጯ ከእግሯ ሥር እየተገነባላት ይገኛል።