Carl Barron Plaza ለረጅም ጊዜ በCentral Square ውስጥ በጣም አስፈላጊው የሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ ሆኖ ቆይቷል። አሁን በCambridge ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ እቅድ እና ኢንቨስትመንት ምክንያት ይህ የማኅበረሰቡ መሠረታዊ ምሰሶ ደኅንነቱ ወደተጠበቀ፣ ደማቅ እና የበለጠ ተቀባይነት ወዳለው መዳረሻ እየተቀየረ ይገኛል።
ጥንቃቄ የተሞላበት የትብብር ሂደት
Carl Barron Plazaን እና በአቅራቢያው ያለውን MBTA የአውቶብስ ተርሚናልን እንደገና ዲዛይን ማድረግ ሂደቱ ቀላል አልነበረም፤ ይህ የዓመታት ጥንቃቄ የተሞላበት እቅድ፣ የቴክኒክ እውቀት እና የትብብር ውጤት ነው። የከተማው ሠራተኞች ከአማካሪዎች፣ ከCentral Square Business Improvement District (BID፣ የCentral Square የንግድ ሥራ ልማት ዲስትሪክት) እንዲሁም ትልቅ ቁጥር ካላቸው የማኅበረሰብ ድምጾች ጋር በመተባበር እያንዳንዱ ዝርዝር ሁኔታ የዕለት ተዕለት ተጠቃሚዎችን እንዲሁም ለCentral Square ያለውን ሰፊ ራዕይ የሚያሟላ መሆኑን አረጋግጠዋል።
አስተዳደሩ መጀመሪያውኑ ነዋሪዎችን እና ንግድ ድርጅቶችን ማዳመጥ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል። የተሰጠው ግብረመልስ ከፕላዛው ስፋት ጀምሮ እስከ መቀመጫ አቀማመጥ፣ የመሬት ገጽታ ዝግጅት እና የአውቶብስ መጠለያዎች ድረስ ሁሉንም ነገር ቅርጽ እንዲይዝ አድርጓል። ይህ ለማኅበረሰብ ቅድሚያ የመስጠት ትኩረት፣ በከተማው ሀብት እና በሠራተኞች ድጋፍ የተደገፈ በመሆኑ፣ ተግባራዊነትን ከኪነ ጥበብ ጋር ያዋሃደ ሚዛናዊ ዲዛይን ፈጥሯል።
በቦታው እና በሰዎች ላይ የተደረገ ኢንቨስትመንት
የከተማው አስተዳደር በዚህ ፕሮጀክት ላይ ኢንቨስት ሲያደርግ ዓላማው አዲስ የአስፋልት መንገድ እና የአውቶብስ መጠለያዎች ብቻ ለመሥራት ሳይሆን፣ Central Square ንቁ እንቅስቃሴ የሚኖርበት ቦታ እንዲሆን ማድረግ ነው። የተስፋፋው ፕላዛ የእግረኛ ፍሰትን ለማቅለል፣ የአውቶብስ ዝውውሮችን ለማቅለል እና ከተራ ውይይቶች እስከ ዋና ዋና የባህል ዝግጅቶች ድረስ ማስተናገድ የሚችሉ ተለዋዋጭ የሕዝብ ቦታዎችን ለማቅረብ ታስቦ የተሠራ ነው።
በከተማ አስተዳደሩ ፋይናንስ እና ቁጥጥር አማካኝነት ሊተገበሩ የቻሉ አንዳንድ ገጽታዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- የተስፋፋ የሕዝብ ቦታ፦ ፕላዛው በከፍተኛ ሁኔታ የሰፋ ሲሆን፣ ይህም አስቸጋሪ የመንገድ መሻገሪያዎች እንዲወገዱ እና የአውቶብስ ተርሚናሉ በአደባባዩ መሃል እንዲኖር አድርጎ አዋህዶ ይዟል።
- ዘመናዊ መገልገያዎች፦ ፕላዛው ከውኃ መሙያ ጣቢያዎች እና የሕዝብ ዋይፋይ ጀምሮ እስከ ዘላቂ የቆሻሻ እና ሪሳይክል ማድረጊያ መሠረተ ልማቶች ድረስ በውስጡ ይዞ፣ ለረጅም ጊዜ የዕለት ተዕለት አገልግሎት የተዘጋጀ ነው።
- ዘመናዊ መብራት እና ገጽታዎች፦ ኃይል ቆጣቢ፣ ለእግረኞች ተስማሚ የኤል.ኢ.ዲ መብራቶች፣ ለሁሉም ተደራሽ የሆኑ የእግረኛ መንገዶች እና ለረጅም ጊዜ ገጽታው ውበቱን ጠብቆ እንዲቆይ የሚያደርጉት የቁሳቁስ ምርጫዎች የከተማ አስተዳደሩ ለደኅንነት እና ጥራት ያለውን ትኩረት ያንጽባርቃሉ።
- አረንጓዴ ዲዛይን፦ የፕላዛው ዛፎች አሁን ካሉት በእጥፍ የሚበልጡ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜ ጤንነታቸውን ጠብቆ ለማቆየትም በተራቀቀ የአፈር ሥርዓት፣ የመንገድ ንጣፎች እና መስኖ ሥርዓቶች ይደገፋሉ።
The Ribbon፦ የCentral Square ምልክት
ከፕሮጀክቱ በጣም ልዩ የሆኑ ገጽታዎች አንዱ «The Ribbon» የተሰኘው ሲሆን፣ የከተማው አስተዳደር ሥነ ጥበብን ከሕዝባዊ መሠረተ ልማት የማዋሃድ ያለውን ቁርጠኝነት ያንጸባርቃል። ይህ የቅርጻ ቅርጽ አካል ተጠምዝዞ የፕላዛውን ሁለቱን ክፍሎች የሚያዋህድ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ እንደ መቀመጫነት፣ የብርሃን ምንጭነት እና የተለያዩ ትርዒቶች የሚዘጋጁበት ስፍራም በመሆን ያገለግላል።
ከCambridge Arts Council (የCambridge ሥነ ጥበብ ምክር ቤት) ጋር በመተባበር፣ የከተማ አስተዳደሩ Ribbonን እንዲቀርጽ እና ቀለም እንዲቀባ የአካባቢውን አርቲስት Sophy Tuttleን የቀጠረ ሲሆን፣ ይህም ከCentral Square የፈጠራ ባህሪ ጋር እንዲጣጣም አድርጎታል። ይህ ተግባራዊ የከተማ ዲዛይን አካል ብቻ ሳይሆን፣ በባህል እና በማኅበረሰብ ማንነት ላይ ያለውን የከተማ አስተዳደሩን ኢንቨስትመንት የሚያሳይ ምልክትም ሆኗል።
ትራንዚትን እና ግንኙነትን መደገፍ
በድጋሚ የተሠራው ዲዛይን ተመላላሽ ተሳፋሪዎች የሚኖራቸውን ተሞክሮ ለማሻሻል፣ የከተማ አስተዳደሩ ከMBTA ጋር በጥብቅ እየሠራ መሆኑን ያሳያል። አዳዲሶቹ የአውቶብስ መጠለያዎች ፈጣን መረጃዎችን፣ ከአየር ንብረት ሁኔታዎች መጠለል የሚያስችሉ ጥላዎችን እንዲሁም ለMBTA ሠራተኞች የተዘጋጁ የሥራ ቦታዎችን ይሰጣሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አዲስ የተሠራው የተለየ የብስክሌት መንገድ River Street ላይ የሚገኘውን የተጠበቀ የብስክሌት መንገድ Massachusetts Avenue ላይ ቀድመው ከነበሩ የታቀዱ መንገዶች ጋር ያለ ምንም መቆራረጥ ያገናኛል።
የCambridgeን እሴቶች የሚያንጸባርቅ ፕሮጀክት
የዚህ ፕሮጀክት እያንዳንዱ ዝርዝር ከመንገድ ድንጋዮቹ እስከ ችግኝ ተከላው ድረስ የከተማው አስተዳደር በተደራሽነት፣ ዘላቂ ልማት እና ማኅበረሰብ ላይ ያተኮረ ዲዛይን ለመሥራት ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት ያንጸባርቃል። የከተማው አስተዳደር በCarl Barron Plaza ላይ ኢንቨስት ሲያደርግ፣ መሠረተ ልማትን እያሻሻለ ብቻ ሳይሆን፣ Cambridge ያሏትን የፈጠራ፣ የሁሉን አቀፍነት እና የባህል ሕያውነት እሴቶች የሚያንጸባርቅ የዜጎች ቦታ እየቀረጸ ነው።
የከተማው አስተዳደር መሪዎች እንደገለጹት፦ «ይህ ፕሮጀክት የCentral Squareን ልብ የሚያነቃቃ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ተቀባይነት ያለው እና ከማኅበረሰባችን ሕይወት ጋር ሙሉ በሙሉ የተዋሃደ ቦታን ይፈጥራል። በቦታው ላይ እንደተደረገው ሁሉ በሰዎች ላይም የተደረገ ኢንቨስትመንት ነው።»
Carl Barron Plaza ሲጠናቀቅ በጥንቃቄ የታሰበ የከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት፣ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞች እና ቁርጠኛ የማኅበረሰብ ትብብር ሊያሳኩ ለሚችሏቸው ነገር በሙሉ ማስረጃ ሆኖ ይቆማል፤ ለCambridge ማኅበረሰብ በሙሉ እውነተኛ የሕዝብ አደባባይ ይሆናል።