ከCity Manager Yi-An Huang ጋር የተደረገ ጥያቄና መልስ
2026 ሴፕቴምበር 3, ሐሙስ
በዚህ ጥያቄና መልስ የCity Manager Yi-An Huang የCambridge የ2027 የበጀት ዓመት (FY) የሥራ ማስኬጃ እና የካፒታል በጀቶችን የሚያስረዱ ሲሆን፣ በጀቶቹን በማዘጋጀት ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩትን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ በወቅቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን ከዘላቂ የፋይናንስ ኃላፊነት ጋር እንዴት እያመጣጠነ እንደሚገኝ ያብራራሉ።
ጥያቄ፦ የዘንድሮው የበጀት ዓመት ለCambridge የበጀት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት ነው። የFY27 (2027 በጀት ዓመትን) ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?
መልስ፦ በCambridge ታሪክ ውስጥ የሥራ ማስኬጃ በጀታችን ከ$1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲያልፍ FY27 የመጀመሪያው ነው። ምንም እንኳን ይህ ትልቅ ስኬት እና አዲስ ምዕራፍ ቢሆንም፣ ከሁሉ በላይ ዋናው ነገር ይህ በጀት ምንን ይዞ እንደመጣና ምንን እንደሚወክል የሚገልጸው ታሪክ ነው ብዬ እምናለሁ።
በጀቱ አቅም ያገናዘበ የመኖሪያ ቤትን፣ የሕፃናት ቅድመ-መደበኛ ትምህርትን፣ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማትን፣ የትራፊክ ደህንነትን፣ የአካባቢ ጥበቃን እና ድጋፍ ለሚሹ ነዋሪዎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማካተት፣ ለማህበረሰባችን በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ያለንን ቁርጠኝነት ያንፀባርቃል። ከዚሁ ጎን ለጎን የበጀቱ ዕድገት ሚዛናዊና ኃላፊነት የተሞላበት እንዲሆን ከCity Council ጋር በትብብር ስንሰራ ቆይተናል።
የጸደቀው የFY27 የሥራ ማስኬጃ በጀት በድምሩ $1.03 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከFY26 ጋር ሲነጻጸር የ4.1 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ይህም ባለፉት አምስት ዓመታት ከተመዘገበው የ6.7 በመቶ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት እና ባለፉት አሥር ዓመታት ከተመዘገበው የ6.1 በመቶ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በእጅጉ ያነሰ ነው።
Boston፣ Worcester እና Springfieldን በመቀላቀል፣ Cambridge በMassachusetts ውስጥ ግዙፍ የሥራ ማስኬጃ በጀት ካላቸው ብቸኛ ከተሞች መካከል አንዷ ሆናለች። ይህ በጀት የምንሰጣቸውን በርካታና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ የነዋሪዎቻችንን መልካም የኑሮ ደረጃ ጠብቆ ለማቆየት እና ለወደፊቱ ዝግጁ ለመሆን ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት የሚያስፈልግ መሆኑን ያሳያል።
ጥያቄ፦ የዘንድሮውን በጀት የቀረጹት የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ምን ነበሩ?
መልስ፦ ይህንን በጀት ያዘጋጀነው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት እና ስጋት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነበር።
የወለድ መጠን መጨመር፣ የንግድና የልማት እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዝ፣ የፌዴራል ፖሊሲ ለውጦች እና የፌዴራል የኮቪድ ድጋፍ ማብቃት በከተማዋ የፋይናንስ ሁኔታ ላይ አሁን ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።
እነዚህ እውነታዎች የሕዝብን ገንዘብ እንዴትና ለምን ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለብን ይበልጥ በጥንቃቄ እንድንወስን አስገድደውናል። ችግሮች ሲከሰቱ ብቻ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ ኢኮኖሚው ምንም ዓይነት ለውጥ ቢያሳይ እንኳ Cambridge በፋይናንስ ጠንካራ ሆና እንድትቀጥል አስቀድመን እየሰራን ነው።
ጥያቄ፦ እነዚህ የኢኮኖሚ ፈተናዎች ቢኖሩም፣ የFY27 በጀት በየትኞቹ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት ማድረጉን ቀጥሏል?
መልስ፦ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች እየተቀያየሩ ቢመጡም፣ ይህ በጀት Cambridgeን ልዩ የሚያደርጓት ዋና ዋና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ኢንቨስት ማድረጉን ይቀጥላል።
ለትምህርት ቤቶች፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሚገኙ መኖሪያ ቤቶች፣ ለትራንስፖርት ደህንነት፣ ለአካባቢ ጥበቃና ዘላቂነት፣ ለሕዝብ መሠረተ ልማቶች እንዲሁም ሕፃናትን፣ ቤተሰቦችን፣ አረጋውያንን እና አቅመ ደካማ ነዋሪዎቻችንን ለሚያገለግሉ መርሃ ግብሮች የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን።
በተመሳሳይ ጊዜ የከተማዋን የወደፊት ፍላጎቶችም በማሰብ የፋይናንስ ዕቅዳችንን እያዘጋጀን እንገኛለን። ይህም የግብር ክፍያን በጥንቃቄ በመቆጣጠር እና ወደፊት ሊያጋጥሙን ለሚችሉ ችግሮች በቂ ዝግጅት በማድረግ፣ በማህበረሰባችን ላይ የምናደርገውን ኢንቨስትመንት አጠናክረን እንድንቀጥል ያስችለናል።
በMassachusetts የሚገኙ ብዙ የከተማ አስተዳደሮች ከንብረት ግብር የሚያገኙት ገቢ ወጪያቸውን መሸፈን ስላልቻለ፣ በProposition 2½ የተደነገገውን ከንብረት ግብር ገደብ በላይ ገቢ እንዲሰበስቡ የሚያስችላቸውን ልዩ ፈቃድ እንዲያጸድቁ መራጮችን እየጠየቁ ይገኛሉ። የሠራተኞች ወጪ መጨመር፣ የጤና መድን ወጪዎች፣ እያረጁ የመጡ መሠረተ ልማቶች፣ የዋጋ ንረት እና የፌዴራል የኮቪድ ድጋፍ በጀት የሚያበቃ መሆኑ በከተማዋ ፋይናንስ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል።
እንደ እድል ሆኖ Cambridge በዚህ ሁኔታ ውስጥ አትገኝም። ለብዙ ዓመታት ፋይናንሳችንን በጥንቃቄ በመምራታችን፣ የንብረት ግብር ገደቡን እንድናልፍ የሚያስችለንን ልዩ ፈቃድ ሳንጠይቅ በማህበረሰባችን ላይ ኢንቨስት ማድረጋችንን መቀጠል ችለናል። ግባችንም ይህንን ጠንካራ የፋይናንስ ሁኔታ ለወደፊቱም እንዲቀጥል ማድረግ ነው።
ጥያቄ፦ የከተማው አስተዳደር የህብረተሰቡን ፍላጎት እያሟላ እነዚህን የፋይናንስ ጫናዎች እንዴት እየተወጣቸው ይገኛል?
መልስ፦ ከCity Council ጋር በቅርበት በመሥራት፣ ለዚህ ዓመት በጀት ጥብቅና የተቀናጀ አሰራርን ተከተልናል።
እያንዳንዱን የበጀት አካል በጥንቃቄ ከመመርመር ባለፈ፣ ወጪ ቆጣቢ አሠራሮችን ለይተን፣ ለአዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ቅድሚያ በመስጠት፣ በጀቱን ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድርባቸው ዘርፎች ላይ እንዲያውል አድርገናል። በተመሳሳይ ጊዜ አስፈላጊ በሆኑ አገልግሎቶች ላይ ኢንቨስት ማድረጋችንን ሳናቋርጥ፣ ለአዳዲስ ፍላጎቶችና ሁኔታዎች አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት አቅማችንን ጠብቀናል።
ጥራት ያለው አገልግሎት የመስጠት አቅማችን የተመሠረተው ተጠያቂነት ባለው የፋይናንስ አስተዳደር ላይ ነው። ዛሬ አስቀድመን የምንወስዳቸው እርምጃዎች፣ Cambridge ለሚመጡት ብዙ ዓመታት የፋይናንስ ጥንካሬዋን ጠብቃ እንድትቀጥል ያግዛሉ።
ጥያቄ፦ ለዚህ ዓመት እቅድ መሥሪያ ቤቶች ምን ዓይነት ማስተካከያዎችን እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል?
መልስ፦ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ነዋሪዎች የሚተማመኑባቸውን የአገልግሎቶች ጥራት ሳይቀንስ፣ ወጪዎችን ለመቀነስ የሚያስችሉ መንገዶችን እንዲያፈላልግ ተጠይቋል።
መሥሪያ ቤቶች ከሥራ ማስኬጃ በጀታቸው ውስጥ ወደ 2.1 በመቶ የሚጠጋ ወጪ የሚቆጥቡበትን አሠራር ለይተዋል። ይህም የሠራተኞች ካሳና ደመወዝ፣ የጤና መድን፣ የጡረታ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የቁሳቁስና ዕቃዎች ወጪዎች፣ እንዲሁም ቀደም ሲል በፌደራል ፈንድ ይሸፈኑ የነበሩ ወጪዎችን በራሳቸው ለመሸፈን የሚደረገውን ጥረት ጨምሮ፣ የማይቀሩ የወጪ ጭማሪዎችን ለማካካስ ያግዛል።
ለምሳሌ ለሥልጠናና ለጉባኤ ከግዛቱ ውጭ የሚደረጉ አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዞዎችን ቢያንስ እስከ ጁን 2027 ድረስ አግደናል። አንድ እርምጃ ብቻውን ለችግሩ መፍትሔ ሊሆን ባይችልም፣ እነዚህ ውሳኔዎች በጋራ የሕዝብ ሀብት በጥንቃቄና በተጠያቂነት ጥቅም ላይ መዋሉን ያረጋግጣሉ።
ጥያቄ፦ የከተማው አስተዳደር የበጀት አሰራሩን ይበልጥ ግልጽ እና ለሁሉም ተራሽ ለማድረግ ምን ዓይነት እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል?
መልስ፦ ቅድሚያ ሰጥተን ከሠራንባቸው ጉዳዮች አንዱ የበጀት ሂደቱን ለመረዳት ቀላል ማድረግና ነዋሪዎች በሂደቱ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን እድል ማሳደግ ነው።
ለዚህም የበጀቱን ህትመት በኦንላይን ለማግኘት፣ ለማሰስና ለመገምገም ቀላል እንዲሆን ሠራተኞቻችን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ኦንላይን የሚገኘውን የበጀት መቃኛ ገጽ) በመጠቀም፣ የከተማዋን የሥራ ማስኬጃ እና የካፒታል በጀቶች በቀላሉ ማሰስና የበጀቱን ዝርዝር መረጃ መመልከት ይችላሉ። የፍለጋ አሠራሩ ስለተሻሻለ፣ የተለያዩ ክፍሎችን ማግኘትና ማሰስ የበለጠ ቀላል ሆኗል።
ከCity Council በተለይም ከFinance Committee (ፋይናንስ ኮሚቴው) ጋር በቅርበት በመሥራት፣ የFY27 በጀትን የተለያዩ ገጽታዎች በስፋት የሚዳስሱ ተከታታይ የሕዝብ ስብሰባዎችን አካሂደናል። እነዚህም ስብሰባዎች የኢኮኖሚ ሁኔታዎች፣ የካፒታል እቅዶች፣በመሥሪያ ቤቶች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እና የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ስልቶች ላይ ያተኮሩ ነበሩ።
በዚህ ዓመትም Budget Office (የበጀት ጽሕፈት ቤቱ) የBudget Walk Through (የበጀት ሂደት ማብራሪያ) ውይይቶችን አስተዋውቋል። እነዚህ ውይይቶች ነዋሪዎች የበጀት ዝግጅት ሂደቱን እንዲረዱ፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች የከተማዋን ወጪ አመዳደብ እንዴት እንደሚወስኑ እንዲገነዘቡ እና ጥያቄዎቻቸውን በቀጥታ ለከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች እንዲያቀርቡ ዕድል ሰጥተዋል።
ግንዛቤ ያለው ህብረተሰብ ለጠንካራ ውሳኔዎች መሰረት ነው። እኛም ነዋሪዎች ኢንቨስት የምናደርግባቸውን ነገሮች ብቻ ሳይሆን፣ ከውሳኔዎቻችን በስተጀርባ ያሉትን ምክንያቶችም እንዲረዱ እንፈልጋለን።
ጥያቄ፦ Cambridge ከዚህ ቀደም ተሰብስቦ በተቀመጠ ገንዘብ ላይ ስትመረኮዝ ቆይታለች። በአሁኑ ወቅት የዚህ ገንዘብ ሁኔታ ምን ይመስላል?
መልስ፦ ባለፉት ዓመታት ከመደበኛው የግብር ገቢ በላይ ሊሰበሰብ የሚችልን ገቢ እና ለተለያዩ ዓላማዎች ያልተመደበ በእጃችን ያለ ገንዘብን በጥንቃቄ በመጠቀም፣ የከተማውን አገልግሎቶች ሳናቋርጥ ያልተጠበቁ ፈተናዎችን መወጣት ችለናል።
በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሁለቱም ሀብቶች ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ታይቶ ወደማያውቅ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ይህም የፋይናንስ ዕቅዳችንን በጥንቃቄና በሥርዓት መምራት እንዳለብን የሚያስታውሰን ጠቃሚ ማሳሰቢያ ነው።
አሁን የምንወስዳቸው ጥንቃቄ የተሞላባቸው እርምጃዎች፣ የፋይናንስ አቅማችንን በሚያስፈልገው መልኩ ለማስተካከል የሚያስችለንን አቅም እንድንጠብቅና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ቢሆኑ እንኳ ነዋሪዎች የሚጠብቁትን ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን አገልግሎቶች ሳናቋርጥ ለማቅረብ በተሻለ አቋም ላይ እንድንገኝ ያደርገናል።
ጥያቄ፦ በዘንድሮው በጀት ውስጥ ለካፒታል እቅድ ምን ያህል ቦታ ተሰጥቶታል?
መልስ፦ የካፒታል እቅድ የከተማችንን የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ደህንነት ለመጠበቅ ከምንጠቀምባቸው እጅግ አስፈላጊ መሳሪያዎች መካከል አንዱ ነው።
የከተማው ማኅበረሰብ የሚያስፈልገው መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረጋችንን እየቀጠልን፣ ዋና ዋና የካፒታል ፕሮጀክቶች የሚሸፍኑትን የሥራ መጠን፣ የሚከናወኑበትን ጊዜ እና የሚከናወኑበትን ቅደም ተከተል በጥንቃቄ በመመርመር፣ ፕሮጀክቶቹ ከከተማዋ የፋይናንስ አቅም ጋር ተመጣጣኝ ሆነው እንዲቀጥሉ አድርገናል።
ለካፒታል ፕሮጀክቶች የሚወሰድ ብድር በዕዳ ክፍያ ምክንያት በወደፊት የሥራ ማስኬጃ በጀቶች ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር፣ አስቀድሞ በጥንቃቄ ማቀድ አስፈላጊ ነው። በዚህ ግምገማ ለወደፊት የሚያስፈልገውን የብድር ክፍያ መጠን መቀነስ ችለናል። በFY26 የበጀት ዓመት የእዳ ክፍያ በ7.7 በመቶ ካደገ በኋላ በFY27 እድገቱን ወደ 4.3 በመቶ ማውረድ ችለናል።
ይህ አካሄድ በወደፊት የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች ላይ ጫና እንዳይፈጠር የሚረዳን ሲሆን፣ በመንገዶች፣ በሕንፃዎች፣ በመናፈሻዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በውኃ መሠረተ ልማት እና ሌሎች ለረጅም ጊዜ ጥቅም በሚሰጡ ንብረቶች ላይ ኢንቨስት ማድረጋችንን እንድንቀጥል ያስችለናል።
ጥያቄ፦ ነዋሪዎች ከዚህ ዓመት በጀት ምን እንዲረዱ ይፈልጋሉ?
መልስ፦ ይህ በጀት በጥንቃቄ የተዘጋጀ፣ የሕዝብ ሀብትን በኃላፊነት የሚመራ እና ለCambridge የወደፊት ሁኔታ ያለንን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ነዋሪዎች እንዲያዩ እመኛለሁ።
ማንኛውንም በጀት ስናዘጋጅ፣ የዛሬን ፍላጎቶች ወደፊት ከሚጠብቁን ኃላፊነቶች ጋር ማመጣጠን ያስፈልጋል። የዚህ ዓመት በጀት Cambridge ለኑሮ ምቹና ማራኪ ከተማ እንድትሆን አስተዋፅዖ በሚያደርጉ አገልግሎቶችና መርሃ ግብሮች ላይ ኢንቨስት ማድረጉን የቀጠለ ሲሆን፣ ከተማዋ ለብዙ ዓመታት ጠንካራ የፋይናንስ አቋም እንዲኖራት የሚያስችሉ በጥንቃቄ የታሰቡ እርምጃዎችንም ያካትታል።
ኃላፊነታችን የዛሬ ነዋሪዎችን ፍላጎት ማሟላት ብቻ ሳይሆን፣ ለተተኪው ትውልድ በፋይናንስ አቋሙ የጸና፣ በአግባቡ የተጠበቀና ለሚመጡ ማንኛውም ሁኔታዎች የተዘጋጀ ማኅበረሰብ ጥሎ ማለፍ ነው።